ወታደራዊ ትዕይንት በትግራይ ክልል

ወታደሮች

በትግራይ ክልል መቀለ ከተማ በርካታ የክልሉ የልዩ ኃይል አባላትና ታጣቂ ሚሊሻዎች በዛሬው ዕለት ወታደራዊ ሰልፍ በማካሄድ ትዕይንት አድርገዋል።

በሰልፉ ላይ የተሳፉት የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላቱ ቀላልና ከባድ የጦር መሳርያዎችን ታጥቀው መታየታቸውን የቢበሲ ዘጋቢ ከመቀለ ገልጿል።

ዛሬ ረፋድ ላይ በክልሉ ዋና ከተማ በመቀለ ጎዳናዎች ላይ በሰልፍ ሲጓዙ የታዩት ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሱት የልዩ ኃይሉ አባላትና ሚሊሻዎች በከተማው ወደሚገኘው ስታድየም በመጓዝ ተሰብስበው ታይተዋል።

በመቀለ ከተደረገው ከዚህ ወታደራዊ የሰልፍ ትዕይንት ባሻገር በሌሎችም የክልሉ ከተሞች ጭምር መደረጉ ለማወቅ ተችሏል።

ቢሆንም ይህ ዛሬ የተካሄደው ወታደራዊ ሰልፍ ዓላማው ምን እንደሆነ የትግራይ ክልል መንግሥት የገለጸው ነገር የለም።

ነገር ግን የትግራይ ክልል የጸጥታ ቢሮ ፌስቡክ ገጹ ላይ "ለሰላም ሲባል ለሚከፈል ዋጋ ሁሌም ዝግጁ ነን" የሚል መልዕክት አስፍሯል።

ቢሮው አክሎም "የአንድ ሕዝብ የሰላሙ ዋስትና ውስጣዊ አቅሙ እንጂ የማንም የውጭ ኃይል ድጋፍና ጥበቃ ሆኖ አያውቅም" ሲል ገልጿል።

የእዚህ ወታደራዊ ትዕይንት ዓላማ ባይገለጽም የትግራይ ክልል መንግሥት ከፌደራሉ መንግሥት በኩል ይደርስብኛል የሚለውን ጫና ለመመከት እየሰራ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

የቀድሞው ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ ከከሰመና የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ ህወሓት ከአዲሱ የብልጽግና ፓርቲ እራሱን ካገለለ በኋላ በፌደራሉ መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል ያለው አለመግባባት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተካረረ መጥቷል።

ወታደሮች

ይህም ሁኔታ በሁለቱ ወገኖች መካከል የኃይል ግጭት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት ከአንዳንድ ወገኖች በኩል ሲነሳ ቆይቷል።

ባለፈው ሳምንት ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር በተደረገ ውይይት ላይ የፌደራል መንግሥት ከትግራይ ክልል ጋር ምንም አይነት ፍጥጫ ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ተናግረዋል።

በዚህም "ማን ነው ማንን የሚወጋው? ለምንድነው የፌደራል መንግሥት ትግራይን የሚወጋው? ይህ የእብደት ንግግር ነው። የፌደራሉ መንግሥት የራሱን ሕዝብ የመውጋት ሃሳብና ፍላጎት ፍጹም የለውም" ብለው ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ነግ ግን የትግራይ ክልል መንግሥት ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት እውነታውን አያንጸባርቅም ሲል አጣጥሎታል።

የትግራይ ክልል መንግሥት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫም "ስልጣን ላይ ያለው አሃዳዊ አምባገነን ቡድን የትግራይ ሕዝብና መንግሥት ምርጫ አካሂዳለሁ በማለቱ ብቻ 'ተዘጋጅቻለሁ፣ እናቶች ያለቅሳሉ፣ የወጣቶች ደም ይፈስሳል፣ መሰረተ ልማት ይወድማል' ሲል በአደባባይ ፎክሯል" ሲል የፌደራል መንግሥቱን ከሷል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በትግራይ ክልልና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ያለው አለመግባባት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው ለነሐሴ ወር የተያዘው አጠቃላይ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወርሽኝ ሰበብ መራዘሙን ተከትሎ ነው።

የምርጫውን መራዘም የትግራይ ክልል የተቃወመው ሲሆን ከሌሎቹ የአገሪቱ ክልሎች ተለይቶ በተናጠል ምርጫውን ለማካሄድ ወስኖ አስፈላጊ የተባሉትን ሥራዎች እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህም ሳቢያ ባለፈው ሳምንትም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በአፋጣኝ እንዲያቆም የሚጠይቅ ደብዳቤ ፅፏል።

በደብዳቤው ላይ ክልሉ በዚህ ውሳኔው የሚገፋ ከሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት "በሕገ መንግሥቱና ሌሎች ሕጎች የተሰጠውን ስልጣን ለመተግበር እንደሚገደድ" ማስጠንቀቁ ይታወሳል።

ወታደሮች